‎የጎፋ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ "ለአረጋዊያን ደህንነትና መብቶች መጠበቅ ሁለንተናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ"በሚል መሪ ቃል በሣውላ ከተማ የውይይት መድረክ አካሄደ።

‎የጎፋ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ "ለአረጋዊያን ደህንነትና መብቶች መጠበቅ ሁለንተናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ"በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የ2018 ዓ/ም የአረጋዊያንን ቀን በሣውላ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

‎የዕለቱ የክብር እንግዳ የጎፋ ዞን አስተዳደር ተወካይና የጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ብላቴ እንደገለፁት አረጋዊያን የደም ዋጋ በመክፈል ሀገርን ከጠላት የተከላከሉ በሙያ ብቃታቸው ለሀገር ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ የዋሉ አሻራቸውን ያስቀመጡ ናቸው በማለት ገልፀዋል።

‎አያይዘውም እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች አቅማቸው ደክሞ ከወጣቱ ሀይል ድጋፍ ሲሹ መስጠትና አረጋዊያንን መደገፍ ግዴታችን ነው ብለው ዛሬ የምናከብረው ቀን ማሰብ ብቻ ሳይሆን የለውጥ የድጋፍ ስልቶችን አቅደን በማውጣት በቀሪ ጊዜያት ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ተናግረዋል።

‎አክለውም ከአረጋዊያን ቀን አከባበር ጋር አብሮ የምናከብረው የቤተሰብ ቀን ማክበራችን ህፃናት በለጋ ዕድሜያቸው እንዲሁም ለአንድ ሀገር መሠረት የሆነውን ቤተሰብ በመልካም ዕሴቶች እንድታነፁ በሆነ ባለሆነ ችግር ከመፍረስ ለመታደግ ነው በማለት ተናግረዋል።

‎የጎፋ ዞን ሴቶቸና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ፀጋነሽ እንግዳ በመድረኩ እንደተናገሩት ዛሬ በዚህ ቀን ሁለት አበይት በዓላትን አቀናጅተን እያከበርን እንገኛለን ብለው የሁለተኛው ቀን ሰው ተኮር በሆነ መልኩ የቤተሰብ ቀንን እናከብራለን ብለዋል።

‎አክለውም ቀኖችን ስናከብር ሰው ተኮር በሆነ መንገድ አረጋዊያንን ከችግራቸው አንፃር በመለየት ምን ዓይነት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በማለት የተለያዩ የድጋፍ ቁሳቁሶችን በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

‎አያይዘውም አረጋዊያን የሚደገፉት ስላጡ ስለሌላቸው ብቻ ሳይሆን የመደገፍ መብት እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በትኩረትና ለውጤት እየተሰራ ይገኛል በማለት ገልፀዋል።

‎የሁለተኛው ቀን የሀገር መሠረት የሆነውን የቤተሰብ ቀንን መሆኑን ተናግረው በአንዳንድ አካባቢዎች ቤተሰብ እየተበተነ በመሆኑ ህፃናት ያለ አሳዳጊ እየቀሩ ወላጆችም ችግር እየደረሰባቸው በመሆኑ ቤተሰብን ማፅናት በሠላም አብሮ መኖር እንዲቻል እንዲታሰብ ተደርጓል ብለዋል።

‎በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጎፋ ዞን አረጋዊያን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ እሸቱ ተስፋዬ እንደተናገሩት አረጋዊያን በማህበር በመደራጀት ከተለያዩ ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት ጋር በመተባበር አቅመ ደካማ ለሆኑ አረጋዊያን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በመርዳት ዘርፈ ብዙ ስራ ተሰርቷል በማለት ገልፀዋል።

‎አያይዘውም በ2018 ዓ/ም በተለያዩ በዓላት አከባበር ላይ ለአረጋዊያን ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያየት ድጋፎችን በማቅረብ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ድጋፎች ተደርጓል ብለዋል።

‎በመጨረሻም ለአረጋዊያን ቤተሰብ አባላት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ውይይቱ ተጠናቋል።