"የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ለክልሉ የፍራፍሬ እና ቡና ልማት ሽፋን እያደገ መምጣት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል " − ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በፍራፍሬ እና በቡና ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በፍራፍሬ፣ በቡናና ሥራስር ተክሎች ልማት ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።
በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ ይበልጥ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በበጋ መስኖና በመኸር እርሻ ከ107 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬና በአትክልት መሸፈኑን ተናግረዋል።
በዋናነትም ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ እና የደጋ ፍራፍሬ እንዲሁም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች መልማታቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በክልሉ ከ60 ሺህ ሄክታር ያልበለጠ የሙዝ ማሳ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፣ በአሁኑ ወቅት በአራት እጥፍ አድጎ ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ለፍራፍሬ እና ቡና ልማት ሽፋን እያደገ መምጣት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ በተያዘው ዓመት በፍራፍሬ የሚለማውን መሬት ሽፋን ለማሳደግ በተያዘ ዕቅድ በተለያዩ አካባቢዎች የሚተከሉ ከ25 ሚሊዮን በላይ የአቮካዶ፣ ማንጎ እና አፕል ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
በማህበር የተደራጁ ወጣቶችም በፍራፍሬ ልማት፣ በግበይትና ማቀነባበር የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።
የቡና ልማትን ከማስፋፋት አንጻር ለቡና ምቹ በሆኑ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ልማቱ እየተከናወነ መሆኑን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድር፣ በጌዴኦ ዞን ቡናን ስፔሻላይዝድ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቡና ልማቱን በጥምር ግብርና በማከናወን የአርሶ አደሩን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራትም ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በክልሉ የቡና ልማቱን ለማስፋት በተያዘው ዕቅድ መሰረት ዘንድሮ ከተዘጋጁ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች አብዛኞቹ ባለፈው ሚያዝያ ወር መተከላቸውን ገልጸው፣ ቀሪዎቹ በቀጣይ ሐምሌ ወር ይተከላሉ ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ለክልሉ የፍራፍሬ እና ቡና ልማት ሽፋን እያደገ መምጣት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል " − ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ