ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የመራጩ ሕዝብ ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል አሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ።

የቦርዱ ሰብሳቢዋ በሰጡት መግለጫ÷ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች የተወዳደሩበት ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ሂደት በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ለዚህም ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ሂደት ያከናወናቸው ዘርፈ ብዙና የተቀናጁ ተግባራት ጠንካራ መሠረት መሆናቸውን አመልክተዋል።

በምርጫው ዕለት የታየው የሕዝብ ተነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ እንደነበርም ጠቁመዋል።

መራጩ ሕዝብ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ድምጹን ሲሰጥ መዋሉን ገልጸው÷ አዲስ አበባን ጨምሮ ረጃጅም ሰልፍ የነበረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እስከ እኩለ ሌሊቱ 6 ሰዓት በማራዘም መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል።

መራጩ ሕዝብ ምሽቱ ሳያሳስበው በትዕግሥት ተሰልፎ ዴሞክራሲያዊ መብቱን መጠቀሙንና ይህም ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ወሳኝ ሚና መጫወቱን አስተድተዋል።