የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታን በይፋ አስጀመሩ
ሰኔ 16/2017 ዓ.ም
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጀጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ቆላ ሙልአቶ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር አካል የሆነውን የአንድ አቅመ ደካማ ዜጋ መኖሪያ ቤት ግንባታን በይፋ አስጀምረዋል።
የቤት ግንባታው በክልሉ እየተተገበረ ያለው የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር አካል እንዲሁም የገጠር ኮሪደር ልማት ፕሮግራም አንዱ አካል መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮግራሙ በተለይ የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸው አቅመ ደካማ ዜጎች ምቹና ጥራቱን የጠበቀ መኖሪያ ቤት በማቅረብ የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በዘንድሮው የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ5 ሺህ በላይ የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች በክልል ደረጃ እንደሚገነቡ የተገለጸ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት የተጀመረው ቤት በዘመናዊ የአፈር ጡብ ቴክኖሎጂ እንደሚገነባ እና በአንድ ወር ውስጥ ተጠናቅቆ ለተጠቃሚው እንደሚተላለፍ ተገልጿል።
ፕሮግራሙ በጎነትን ከቃል ወደ ተግባር በመቀየር የአቅመ ደካማ ወገኖችን የመኖሪያ ችግር ከመፍታት ባለፈ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶችን ለማጠናከር የሚያግዝ ተግባር መሆኑ ተመላክቷል።
የቤቱ ግንባታ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ዘለቀ ዛንባ በተደረገላቸው ድጋፍ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፣ የተገነባላቸው ቤት የኑሮ ሁኔታቸውን በእጅጉ ከማሻሻሉ በተጨማሪ ለልጆቻቸው ትልቅ ተስፋና የተሻለ የወደፊት ሕይወት መሠረት እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህ የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያተኩረው በቤት ግንባታ ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊ ድጋፍና በሕይወት ማዳን ተግባራት ላይም በማተኮር የሚቀጥል ይሆናል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ግንባታን በይፋ አስጀመሩ