ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ 2018 ዓ/ም ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምረዋል
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት 2018 ዓ/ም ክልላዊ የክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ላንቴ ቀበሌ ተካሂዷል ።
ርዕሰ መስተዳድሩ መርሃግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የአካባቢ ደህንነትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታትና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀው፤ ዛሬ የምንተክለው ከናዳ ለመትረፍ፣ ከጎርፍ ለመዳን እና አረንጓዴ ምድር ለትውልድ ለማውረስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልላችን የተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ምድር በእንክብካቤ ጉድለት መታመሟን የሚያሳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለህመሟ መፍትሄው የአረንጓዴ አሻራ ስራን በተደራጀ መልኩ ማከናወን ተራሮችን በማልማት ከስጋት ወደ ሀብት ምንጭ መቀየር እንደሚገባ ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀው፤ በክረምት የአረንጓዴ አሻራ በክልሉ 300 ሚሊዮን የተለያዩ ችግኝ በመትከል ለሀገራዊው ግብ ስኬት ጉልህ አስትዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማፅደቅና ማፅናት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ በተደጋጋሚ በተራራማ አካባቢዎች የሚከሰት ናዳን መከላከል ከመቸውም ጊዜ በላይ የአረንጓዴ አሻራን የህልውና ጉዳይ በማድረግ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስጀማሪነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በኅብረተሰቡ ችግኝ የመትከል ባህል መሰረታዊ ለውጥ በመታየት ላይ መሆኑንም ገልፀው፤ ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ደህንነቱ የተጠበቀ አረንጓዴ ከባቢን ለመጪው ትውልድ ማቆየት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃግብርም በክልሉ የደን ሽፋን ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት 24 በመቶ ማድረሱን ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
መላው የክልሉ ህዝብ፤ ከታዳጊ እስከ አዋቂ በየአካባቢው በተዘጋጁ ችግኝ መትከያ ቦታዎች በክረምት ተከላ በመርሃግብሩ በንቃት በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲያኖሩ ተራራ ርዕሰ መስተዳድሩ ዳግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ 2018 ዓ/ም ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በይፋ አስጀምረዋል