በጎፋ ዞን በጋልማ ከተማ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የመስኖ ፕሮጀክት የካናል ስራ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሄደ።
ሣውላ፦ሰኔ 18/2018 ዓ/ም
በጎፋ ዞን በጋልማ ከተማ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የመስኖ ፕሮጀክት የካናል ስራ ማስጀመሪያ መድረክ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በተገኙበት የቦታ እርክብክብ ተካሂዷል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ እንደተናገሩት ዉሃ አጠርና ቆላማ አካባቢዎችን የጉድጓድ ውሃ በማስቆፈርና የውሃ አማራጮችን በማፈላለግ ለተጠቃሚነቱ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ፕሮጀክት ማሰራት ተችሏል ብለዋል።
አያይዘውም በጋልማ ከተማ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ በደቂቅ አስር ሊትር ማውጣት የሚችል የጉድጓድ ውሃ በማስቆፈር 17 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመስኖ ስራ ለመስራት በዛሬው ቀን ለማስጀመር ተገኝተናል ብለዋል።
ከጉድጓዱ የሚገኘውን ውሃ አርሶ አደሩ በተገቢው ተጠቃሚ እንዲሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚሰራ ተናግረው ግንባታው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ በጋራ ይሰራል በማለት ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ም/ኃላፊና መስኖ ማስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ኢሳይያስ ቢፍቱ በበኩላቸው እንደተናገሩት ይህ ፕሮጀክት የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በ30 ሚሊየን እንደተጠናቀቀ ተናግረው የዛሬው የውሃ መውረጃ ካናል ወደ ማሳ ውሃ ማድረሻ ቦይ ለመስራት ከኮንትራክተሮች ጋር በ35 ሚሊየን ብር ውል በመግባት በአምስት ወር ውስጥ እንዲጠናቀቅ ስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
የጎፋ ዞን መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አጥናፉ አባተ እንደተናገሩት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በዞኑ የመጀመሪያ የሆነውን በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የመስኖ ስራ በጋልማ ከተማ ማስጀመራቸውን ተናግረዋል።
የጋልማ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ተስፋለም ነከረ በበኩላቸው በከተማው የተጀመረው የመስኖ ስራ ለአርሶ አደሮቻችን ትልቅ ተስፋ ሰጭ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያት በድርቅና በውሃ አጠር የሚቸገሩትን በማገዝ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
በጎፋ ዞን በጋልማ ከተማ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የመስኖ ፕሮጀክት የካናል ስራ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሄደ።