የመንግስት ሃብትና ንብረት ውጤታማ በሆነ መልኩ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልለማድረግ የኦዲት ስራን ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ
ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
ቢሮው "የሕዝብና የመንግስት ሃብትን ከብክነትና ከብልሽት እንከላከል" በሚል መሪ ቃል የ2018 የበጀት አመት አፈፃፀም በአርባምንጭ ከተማ ገምግሟል ።
በወቅቱ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ የህዝብን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት እንዲቻል የኦዲት ስራን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ተግባሩን ማጠናከር የሙስና እና ብልሹ አሰራር ተጋላጭነት እንደሚቀንስ የገለፁት አቶ ተፈሪ በዘርፉ የሚከናወኑ ስራዎች በተጠናከረ አግባብ መከናወን እንዳለባቸው አስረድተዋል ።
የሕዝብና የመንግስት ሃብትን ከብክነት መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አውስተው ፣ኦዲተሮች የቁጥጥር ስርዓቱን የማጠናከር ሂደት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል ።
ለዘርፉ ውጤታማ በየተቋማቱ እውቀትና ብቃት ያለዉን የሰው ሀይል ሟሟላት እንደሚገባ የገለፁት አቶ ተፈሪ ፣ለዚህም የሚደረግ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኢንስፔክሽንና የውስጥ ኦዲት ቁጥጥር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ታመነ ታምርሶ በበኩላቸው በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማት የሚቀርብላቸውን የኦዲት ግኝት ለማስተካከል የሚያደርጉት ጥረት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀዋል ።
በቀጣይም ይህንኑ ለማጠናከር የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከር አቶ ታመነ አስረድተዋል ።
በወቅቱ አስተያየታቸውን የሰጡት የመድረኩ ተሳታፊዎች የፋይናንሻልና ክዋኔና የኦዲት ሥራዎችን ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ተዓማኒ ለማድረግ ባለሙያዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በማብቃት አቅማቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በየተቋማቱ በዘርፉ እውቀትና ብቃት ያለዉን የሰው ሀይል መሟላት እንዳለበት ጠቁመው፦ለዚህ ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎችን የመስጠት ተግባር እንዲጠናከር ጠይቀዋል ።
ሀብትን በግልጽነትና በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውሉ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል ።
የመንግስት ሃብትና ንብረት ውጤታማ በሆነ መልኩ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልለማድረግ የኦዲት ስራን ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ