የወተት ሀብትን ወደ ልማት መቀየር የጎፋ ዞን ትኩረት!
በጎፋ ዞን ዛላ ወረዳና ጋልማ ከተማ ያለውን የወተት ምርት አቅም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ውጤት ለመቀየር የተጀመረው ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።
ሰኔ 19/2018 ዓ.ም
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ እና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በዛላ ወረዳና በጋልማ ከተማ የተቋቋመውን የወተት መንደር በመጎብኘት የሚከናወኑ ስራዎችን በቅርብ ተመልክተዋል።
በጉብኝታቸውም የተጀመሩት ተግባራት በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲሆኑ በሁሉም አካላት የተቀናጀ ርብርብ እንዲቀጥል አስፈላጊነቱን ገልጸዋል።
ይህ ተግባር የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግና የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ያለመ ነው ስሉ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ ወጣቶችን በማደራጀት ከፍተኛ የወተት ምርት የሚሰጡ የውጭ ደም ያላቸው ከብቶችን በማስገባት ዘመናዊ የወተት እርባታን ለማስፋፋት በዞኑ አስተዳደር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በጉብኝታቸው ገልፀዋል።
ይህም የወተት ምርትን ከመጨመር ባለፈ የወጣቶችን ተሳትፎ በማጠናከር ዘላቂ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል አቅጣጫ መሆኑን አመላክተዋል።
ለሎች ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ከዚህ ጉብኝት እና ስራ ተሞክሮ በመውሰድ በየአካባቢያቸው ልያሰፉ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የጋልማ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ተስፋለም ነከረ በበኩላቸው፣ በቀጣይ የወተት መሰብሰቢያ፣ መሸጫ እና ፕሮሰሲንግ (እሴት ጨምሮ ወደ ተለያዩ ምርቶች የመቀየር) ማዕከላትን ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ስራ የወተት ምርትን የገበያ ተወዳዳሪ ከማድረጉም በላይ ለአምራቾች የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ ያግዛል በማለትም አክለዋል።
የማህበሩ ተወካይ አቶ ወላሞ ወቆ እንደገለጹት፣ መንግስት ባመቻቸው የስራ ዕድል ፈጠራ አቅርቦት መነሻነት በመደራጀት ወደ ምርታማ ስራ መግባታቸው ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁመው፣ ድጋፉ በቀጣይነት ከቀጠለ የበለጠ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ገልጸዋል።
በተጨማሪ አቶ አብርሃም ባጌ በአካባቢው ቀደም ሲል በስሙና በጥራቱ ይታወቅ የነበረውን "የዛሎ ማሶ" ብራንድ እንደገና ለማንሳትና ወደ ገበያ ለመመለስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የአካባቢውን የወተት ምርቶች በብራንድ በማቅረብ የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ትልቅ እድል ይፈጥራል በማለትም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በዛላ ወረዳና በጋልማ ከተማ እየተካሄደ ያለው የወተት ልማት ተነሳሽነት የአካባቢውን የተፈጥሮ አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር፣ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የእሴት ጭማሪ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና የጎፋ ዞንን በወተት ምርት ተወዳዳሪ ለማድረግ ተስፋ ሰጪ እርምጃ መሆኑን ያሳያል።
የወተት ሀብትን ወደ ልማት መቀየር የጎፋ ዞን ትኩረት!