በጎፋ ዞን በደምባ ጎፋ ወረዳ በዛንጋ አዋንዴ ቀበሌ በበንዲ ተፋሰሰ በሰዎች ለሰዎች ግብረ-ሰናይ ድርጅት የተራቆቱ ተራሮችን የማልማት ችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት ስራ ምልከታ ተደረገ።

‎ሣውላ፦ሰኔ 22/2018 ዓ/ም

‎የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ የተመራው የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በደምባ ጎፋ ወረዳ በዛንጋ አዋንዴ ቀበሌ በበንዲ ተፋሰሰ በሰዎች ለሰዎች ግብረ-ሰናይ ድርጅት የተራቆቱ ተራሮች የማልማት ችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት ስራ ምልከታ በጋራ አድርገዋል።

‎የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ እንደተናገሩት እንደ ሀገር ካርበን እጅጉን እየጨመረ በመምጣቱ በየአካባቢው የተፈጥሮ አደጋዎች እየተከሰቱ ይገኛል ብለው እኛም የዚህ ችግር ተጎጂዎች ነን ብለዋል።

‎አያይዘውም በዛንጋ አዋንዴ ቀበሌ በበንዲ ተፋሰስ በሰዎች ለሰዎች ግብረ-ሰናይ ድርጅት አንድ ተራራ የማልማት ስራ የተጀመረው ድርጅቱ ማህበረሰቡ በተፋሰሰ በተለየው ተራራ ላይ ችግኞችን በመትከል በማልማት ከሚገኘው የኦክስጂን አየር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል በማለት ተናግረዋል።

‎በተጨማሪም ተራሮችን የማልበስ ስራ በዚህ ቀበሌ ብቻ የሚሰራ እንዳልሆነ ተናግረው በሁሉም የዞኑ መዋቅሮች ማህበረሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

‎የጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፌ በበኩላቸው እንደተናገሩት የግብርና ስራ ዘርፈ ብዙ ቢሆንም የመጀመሪያው አካባቢን ማልማትና ተራሮችን በደን መሸፈነ እንደሆነ ገልፀዋል።

‎አክለውም እንደ ዞን 27 ሺህ ሄክታር ለማልማት በማቀድ እየተሰራ እንዳለ ተናግረው በረጂና በማህበረሰብ ተሳትፎ ትልልቅ ተራራ ልማቶች የችግኝ ተከላዎች በሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ይተገበራል ብለዋል።

‎ፕሮጀክት አስተዳዳሪ አቶ በረከት ጋሻበዛ የካርበን ልቀት ለመቀነስ ሰዎች ለሰዎች ፕሮጀክት በአካባቢ እየተፈጠረ ያለውን የተራራ መራቆት እንዲሁም የወደፊት ስጋትን ለመከላከል ከረጂ ድርጅቶች በኩል ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

‎የደምባ ጎፋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አራሹ አበበ እንደተናገሩት በማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ የተራቆቱ መሬቶችን እና አለግባብ ተጨፍጭፈው ገላጣ የሆኑ ተራሮችን በችግኝ ተከላ በማካለል እንዲሁም በችግኝ በመሸፈን እና በመንከባከብ ከእንሰሳትና ከሰው በመጠበቅ እንደሚለማ ተናግረዋል።

‎አንዳንድ ያነጋገርናቸው የአካባቢ ነዋሪዎች ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በቀበሌው በመግባቱ ተደስተው የማህበረሰብ ተሳትፎ ላይ በንቃት እንሳተፋለን በማለት ተናግረዋል።