*****
( የዕለቱ መልዕክት)
የአንድ ሀገር ህልውና እና ጥንካሬ መሰረቱ የህዝቡ አንድነት፤ ትብብርና ቁርጠኝነት ነው። ሰኞ ዕለት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሳየው ታሪካዊ ተሳትፎ የዚሁ እውነት ህያው ማረጋገጫ ነው።
የራሳቸውን ፍላጎት በራሳቸው ለመወሰን፣ የወደፊት የ5 ዓመት እጣ ፈንታቸውን በራሳቸዉ እጅ ለመጻፍ ከ54 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
ይህ ቁጥር ዝም ብሎ ስታቲስቲክስ ሳይሆን የህዝባችንን ፍጹም መነሳሳትና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ያለውን ጽኑ አቋም ፍንትው አድርጎ ያሳየ ታላቅ ኩራት ነው።
ከወዲያ ማዶ ሆኖ ማውራት ለነጋሪው ቀላል ነው፤ እንደሚባለው ሀገርን ማቅናትና ዲሞክራሲን መገንባት በወሬ ሳይሆን በተግባርና በጽናት የሚገኝ መሆኑን መራጩ ህዝብ በግልጽ አስመስክሯል።
ማለዳው ገና ሳይቀድ፣ ንጋቱ ሳይተካ ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያው የተሰለፈው ህዝብ ያሳየው ትዕግስት የሚደነቅ ነው። የጠዋቱ ቅዝቃዜና ብርድ፣ የቀትሩ አስገዳጅ ጸሀይም ሆነ ከባዱ ዝናብ ሳይበግረው፤ ረጃጅም ሰልፎችንና የአካል ድካምን ተቋቁሞ ከሌሊት እስከ ሌሊት የቆመው ለራሱ ጥቅም ብቻ አልነበረም።
ይልቁንም፣ "የቆረጠ አይመለስም" እንደሚባለው የነገዋን ኢትዮጵያ ለማጽናት፣ ጠንካራና የማይናወጥ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ባለው ጽኑ ህልም እንጂ።
ይህ ጽናት ህዝቡ የሀገር ጉዳይ ከምንም ነገር እንደሚቀድም ብሄራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት የሚከበሩት ደግሞ በዜጎች ንቁ ተሳትፎ መሆኑን ያሳየበት የታሪክ አሻራ ነው።
ህዝቡ ፍላጎቱን በምርጫ ካርዱ መግለጹ የዲሞክራሲ ባህላችን ከቃል ባለፈ ወደ ተግባር እየተሸጋገረ ለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ ነው። "ስልጣን የህዝብ ነው" የሚለው መርህ መሬት የረገጠው፣ ዜጎች ያለ ምንም ስጋትና በከፍተኛ ተነሳሽነት መብታቸውን ሲጠቀሙ ነው።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው ታሪካዊ ክስተት ኢትዮጵያ መምረጧን ብቻ ሳይሆን በልጆቿ ጽናት መጽናቷንና ወደፊት መራመዷን ጭምር ያበሰረ ነው።
አሁን የምርጫው ውጤት እስኪገለጽ ድረስ ባለው ወቅት፣ ሁላችንም ልባችንን ሰብስበን፣ የተጀመረውን የሰላምና የዲሞክራሲ ጉዞ ማገዝ ይኖርብናል። ምክንያቱም "በአንድ እጅ አያጨበጭቡም" እና ሀገርን የመስራት፣ ተቋማትን የማጠንከርና ሰላምን የማስፈን ኃላፊነት የሁላችንም የጋራ የቤት ስራ ነው።
የህዝብ ስልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጠው በዚህ መልኩ በካርድ በሚሰጥ ድምጽ እና በሚታይ ቁርጠኝነት ነው። ትናንት የፈሰሰው ድካምና መስዋዕትነት፣ ዛሬ ለምናየው የነጻነት አየር መሰረት ሆኗል። ህዝባችን ያሳየው ታላቅ የሀገር ፍቅር የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት መተኪያ የሌለው የሞራል ስንቅ ነው።
አሁን ኑ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በምርጫ ካርዳችን ያጸናናትን ሀገር በስራችንና በአንድነታችን እንገንባት።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጽናትና ፍቅር ለዘላለም ትኑር!
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል
በካርዳችን ያጸናናትን ሀገር በአንድነታችን እንገንባት