የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሰላማዊ እና በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ በጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በተገኙበት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተገምግሟል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሰላማዊ እና በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ በዞኑ የተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን የማጠቃለያ ግምገማ አካሂደዋል።

በግምገማው ወቅት በዞን ማዕከል በሚገኙ ሶስት የፈተና ጣቢያዎች በመስመር ላይ (Online) ለሚሰጠው ፈተና የሚያስፈልጉ የቴክኒክ፣ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተገቢው ሁኔታ መጠናቀቃቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም በወረቀት ለሚፈተኑ ተማሪዎች ወደ ፈተና ማዕከላት የሚደረገው የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲሁም የፀጥታ ጥበቃ በቅንጅት እንዲፈጸም በሁሉም ተቋማት የተጠናከረ ትብብር እንዲኖር አቅጣጫ ተሰጥቷል።

ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ፈተናው የተማሪዎች የዓመታት ጥረትና የወደፊት ትምህርት መሠረት በመሆኑ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በሙሉ በመወጣት ፈተናው ያለምንም እክል እንዲጠናቀቅ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በተለይም ተፈታኝ ተማሪዎችን በሰዓቱ እና በደህንነት ወደ ፈተና ማዕከላት ለማጓጓዝ የትራንስፖርት አቅርቦቱ በተገቢው ሁኔታ መደራጀት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የፈተና አሰጣጥ፣ የፀጥታ ጥበቃ እና የቴክኒክ ድጋፍ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ እንዲመሩ ቴክኒክ ኮሚቴዎች በንቃትና በኃላፊነት እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በጎፋ ዞን አስተዳደር በበኩሉ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሰላም፣ በፍትሃዊነት እና በተሟላ ዝግጅት እንዲጠናቀቅ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሥራውን በትኩረት እየተመራ መሆኑ ተገልጿል።