የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሣውላ ካምፓስ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን በሣውላ ከተማ አስመረቀ።
ሰኔ 21/2018 ዓ.ም
የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሣውላ ካምፓስ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በሳምንት መጨረሻ መረሃ ግብር ያሰለጠናቸዉን ተማሪዎችን ከፍተኛ የክልል፣የዞን አመራሮችና የዩኒቨርስቲ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት አስመርቋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ቦጋለ ፈይሳ በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ የ9ኛ ዙር የምርቃ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት ከአንድ የጉድጓድ ምንጭ በመቀዳት የፍጥረትን ጥማት እንደሚያረካ ሁሉ በትጋትና በፅናት እንደምታገለግሉ እምነት አለኝ ብለዋል።
አያይዘውም ዛሬ ዕውቀታችሁ ዕውቅና አግኝቶ ወደ የምታገለግሉት ሕዝብ ስትመለሱ የምትቀዱ ምንጮች እንድትሆኑና በስነ-ምግባር በመታነፅ እንድታገለግሉ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢንጂነር አብዴላ ከማል በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ካሉ ተቋማት ትልቁና የምርምር ማዕከል መሆኑን ገልፀው በተለያዩ ዞኖች ቅርንጫፍ ካምፓሶችን በመክፈት የትምህርት ምህዳሩን አስፍቷል ብለዋል።
አክለውም ዩኒቨርስቲያችን በዕውቀትና በምርምር በፈጠራ እና በማህበረሰብ አገልግሎት የተቀረፁ ዜጎችን ለሀገር ለማበርከት ያለውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ ዛሬ የምናስመርቃቸው ተመራቂ ተማሪዎች የዚህ ተልዕኮ ሕያው ውጤት ናቸው በማለት ገልፀዋል።
በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የሣውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዶሳ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት መንግስት ሁሉም ዜጎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት የጎፋና አካባቢዋ ህዝቦች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል በአቅራቢያ ያለማገኘታቸውን በማረጋገጥ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ቦርድ ሴኔትና የበላይ አመራሮች በ2008 ዓ/ም የሳውላ ካምፓስ ልደትን እውን በማድረጋቸው እነሆ ዛሬ ለ9ኛ ዙር ተማሪዎችን ለማስመረቅ በቅቷል በማለት ገልፀዋል።
አያይዘውም የዛሬ ምሩቃንን 109 የመጀመሪያ ዲግሪና 12 የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ለምረቃ መብቃታቸውን በመድረኩ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በትምህርት ውጤታቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ከየትምህርት ክፍሉ የሜዳሊያና የወርቅ ሽልማት በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።
የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሣውላ ካምፓስ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን በሣውላ ከተማ አስመረቀ።