የ2018 ዓ.ም የገቢ አሰባሰብና የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ዞናዊ ንቅናቄ መድረክ በሣውላ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ሰኔ 27/2018 ዓ.ም
የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ እና ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ በጋራ ያዘጋጁት የ2018 የግብር ዘመን የገቢ አሰባሰብና የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ስራዎችን ለማፋጠን የታለመ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ በሣውላ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
መድረኩን የከፈቱት የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ፤ የመንግስት ጥንካሬ የሚለካው የአካባቢውን የገቢ አቅም በሙሉ በመጠቀም ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣንና ተገቢ ምላሽ መስጠት ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ምናሴ ገለፃ፣ በጎፋ ዞን የገቢ አሰባሰብ አቅም ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ የኤክስፖርት ሰብሎችን በስፋትና በጥራት በማምረት የገቢ ምንጮችን ማስፋት፣ ያሉ ውስንነቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አቶ ምናሴ አክለውም የገቢ አሰባሰብ ስራውን ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ቀድሞ በማጠናቀቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን እና የህዝቡን ፍላጎት ለመመለስ እንደሚያስችል ገልጸው፣ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር የገቢ አቅምን ማጠናከር እና የንግድ ፈቃድ ዕድሳትን በህጋዊ ስርዓት ማከናወን የሁሉም ተቋማት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የጎፋ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ጉጃ፣ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ ለማድረግ ከወረቀት ወደ ዲጂታል የሚቀየር ስርዓት በስፋት እየተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ በ2018 የግብር ዘመን ከዚህ ቀደም በሶስት ደረጃ የነበረው የግብር ከፋይ ምደባ ወደ ሁለት ደረጃዎች ብቻ ተቀይሯል። በዚህም 487 የደረጃ "ሀ" እና 10,563 የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች እንዳሉ በመጠቆም፣ ቀሪውን 25 በመቶ የገቢ አሰባሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጠንካራ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በመድረኩ የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ፣የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይሁን ደምሴ የዞን አመራሮች፣የወረዳ/ከተማ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት፣የገቢዎች እና የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የ2018 ዓ.ም የገቢ አሰባሰብና የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ዞናዊ ንቅናቄ መድረክ በሣውላ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።