የጎፋ ዞን ልማት ማህበር የግማሽ ሚሊዮን አባላት የማፍራት ንቅናቄ በሣውላ ከተማ በይፋ ተጀመረ
ሣውላ፣ ሐምሌ 2/2018 ዓ.ም
የጎፋ ዞን ልማት ማህበር የፋይናንስ አቅሙን በማጠናከር በዞኑ ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን ያለመ የግማሽ ሚሊዮን አባላትን የማፍራት ንቅናቄ በሣውላ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
በንቅናቄው ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ እንደገለጹት፣ የጎፋ ዞን ልማት ማህበር በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማትና በሌሎች የልማት ዘርፎች የጀመራቸውን ተግባራት በማጠናከር ውጤታማ ተቋም ለመሆን በትጋት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ኢንጂነር ዳግማዊ ገለጻ፣ ማህበሩ ዘላቂ የገቢ ምንጮችን ለመፍጠር በሣውላ ከተማ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ በቅርቡም ከሣውላ ከተማ አስተዳደር በተገኘ መሬት ላይ የራሱን የንግድ ማዕከል ሕንፃ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ማህበሩን በአስተዳደር፣ በፋይናንስና በተቋማዊ አቅም በማጠናከር ወደ ጠንካራ ኮርፖሬት ተቋም ለማሳደግ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
የጎፋ ዞን ተወላጆች፣ የዞኑ ነዋሪዎችና የጎፋ ወዳጆች በሙሉ የልማት ማህበሩ አባል በመሆን የእኔነት ስሜታቸውን እንዲያጠናክሩ፣ ለዞኑ ዘላቂ ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ነፃነት ገመዳ እንደተናገሩት ልማት ማህበሩ በቅርቡ የአመራር እና የአደረጃጀት ለውጥ በማካሄድ ውጤታማ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ኢንጂነር ነፃነት አክለው የልማት ማህበሩን የገቢ አቅም ለማሳደግ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናገረው የገቢ አቅማችንን ይበልጥ ለማሳደግ አባላትን የማፍራት ዘመቻ በልዩ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በመድረኩ በልማት ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ በኢንጂነር ነፃነት ገመዳ አማካኝነት በልማት ማህበሩ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ስራዎች አፈፃፀም ሪፖርት እና የንቅናቄውን ዘመቻ ዕቅድ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
በንቅናቄ መድረኩ የጎፋ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ሀብታምነሽ ግራዝማች፣የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ፣የጎፋ ዞን የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይሁን ደምሴን ጨምሮ፣የዞን፣የወረዳ አመራሮች እና የልማት ማህበር ቅ/ጽ/ቤት ስራ አስኪያጆች እና አጋር አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የጎፋ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት
የጎፋ ዞን ልማት ማህበር የግማሽ ሚሊዮን አባላት የማፍራት ንቅናቄ በሣውላ ከተማ በይፋ ተጀመረ