በጎፋ ዞን የኮ-ዋሽ ፕሮግራም የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በቡልቂ ከተማ ተካሄደ

ሣውላ፣ ሐምሌ 2/2018 ዓ.ም

የጎፋ ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ በገዜ ጎፋና በመሎ ጋዳ ወረዳዎች የሚተገበረውን የኮ-ዋሽ (COWASH) ፕሮግራም የ2018 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቡልቂ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የስቲሪንግ ኮሚቴ አባላት፣ የወረዳዎች የውሃና ኢነርጂ ባለሙያዎች፣ የፕሮግራሙ ፎካል አካላትና አጋር ተቋማት ተሳትፈዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የዞኑ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንቲ ጎሽሜ መድረኩን ሲከፍቱ፣ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ዓላማ፣ በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለማህበረሰቡ ጥቅም እንዲውሉ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ቁርጠኝነት፣ ግልጽ ተጠያቂነትና የተቀናጀ የሥራ ቅንጅት ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አያይዘውም፣ የኮ-ዋሽ ፕሮግራሙ የንጹህ የመጠጥ ውሃና የንጽህና አገልግሎትን በማስፋፋት የማህበረሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከር የታዩ ክፍተቶችን በወቅቱ ማረም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም በዞናችን በሁለቱ መዋቅሮች የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትንና በትምህርት ቤቶች እና ጤና ተቋማት ቤቶች የመፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት የህዝቡን ጥያቄ በተግባር እየመለሰ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የጎፋ ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ በኃይሉ ታገሰ በበኩላቸው፣ የኮ-ዋሽ ፕሮግራሙ በገዜ ጎፋና በመሎ ጋዳ ወረዳዎች በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በትምህርት ቤቶችና በጤና ተቋማት የውሃና የንጽህና አገልግሎት ማሻሻያ እንዲሁም በመፀዳጃ ቤት ግንባታ ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

አክለውም፣ በሁለቱ ወረዳዎች በትምህርት፣ በጤናና በማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ የፕሮግራሙ ሥራዎችን ለማከናወን ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልጸው፣ ይህም በአካባቢው የውሃና የንጽህና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የስቲሪንግ ኮሚቴ አባላትና የፕሮግራሙ ፎካል አካላት በበኩላቸው፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በወቅቱና በጥራት እንዲጠናቀቁ በጋራ መስራት እንዳለባቸው በመስማማት፣ በ2019 በጀት ዓመት የቀሩ ሥራዎችን በቅድሚያ በማጠናቀቅ የፕሮግራሙን ዘላቂነትና ውጤታማነት ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም፣ በ2019 በጀት ዓመት ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በቅድሚያ ለማጠናቀቅ፣ የተጠናቀቁ ሥራዎችን ለማህበረሰቡ በይፋ በማስረከብ እና የፕሮግራሙን ዘላቂነት በማረጋገጥ ሁሉም ተዋናዮች በቅንጅት እንዲሰሩ በመስማማት የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል።