"የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን እውን ለማድረግ ሁሉም ተቋማት በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል" አሉ አቶ ይሁን ደምሴ
ሣውላ!ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
የጎፋ ዞን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በሣውላ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ሴክቶሪያል ጉባኤ በተለያዩ ውሳኔዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ተጠናቋል።
በጉባኤው የመምሪያው የዕቅድ፣ በጀትና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ቃለመለኮት ሰይፉ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምንና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድን በዝርዝር አቅርበዋል።
በሪፖርቱም መምሪያው በ2018 በጀት ዓመት የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን፣ የመንግስት አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን ለማስፋፋት፣ የመረጃና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ለማጠናከር እንዲሁም የተቋማትን የዲጂታል አሰራር ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።
በሪፖርቱ ላይ ከተሳታፊዎች የቀረቡ ገንቢ ሀሳቦችና አስተያየቶች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በተለይም የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር፣ ተቋማዊ ድጋፍና ክትትልን ማሻሻል፣ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ አቅርቦትን ማጠናከር እንዲሁም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለሁሉም ብቁ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመድረኩ የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይሁን ደምሴ እንደገለጹት፣ የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይ መረጃና ቴክኖሎጂን የልማት ማፋጠኛ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂና ውጤታማ የመንግስት አገልግሎት ለመገንባት የተያዘ አገራዊ አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ራዕይ በጎፋ ዞን እውን ለማድረግ ሁሉም ተቋማት የተቀናጀ አሰራርን በማጠናከር በኃላፊነትና በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አቶ ይሁን አክለውም፣ ቴክኖሎጂ የመንግስት አገልግሎቶችን ለዜጎች ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ተደራሽ ከማድረጉ ባሻገር የጊዜ፣ የጉልበትና የፋይናንስ ወጪን በእጅጉ እንደሚቀንስ ገልጸው፣ በተለይም የዙም (Zoom) እና ሌሎች የቪዲዮ ኮንፈረንስ መድረኮችን በስፋት በመጠቀም በየጊዜው የሚካሄዱ የሥራ ስብሰባዎችንና ውይይቶችን በወጪ ቆጣቢ፣ ፈጣንና ውጤታማ መንገድ ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይ መሠረታዊ ግብዓት በመሆኑ ሁሉም ብቁ ዜጎች በፍጥነት እንዲመዘገቡ የሁሉም ተቋማት የጋራ ኃላፊነት ነው ብለዋል።
የዲጂታል ሽግግር ሥራዎች የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም ተቋማት የጋራ ተልዕኮ ናቸው፤ በመሆኑም በቅንጅት በመስራት ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት ማቅረብ ይገባናል" ብለዋል።
የጎፋ ዞን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ፋይሌ በበኩላቸው፣ መምሪያው በ2019 በጀት ዓመት የዲጂታል ሽግግር ሥራዎችን በተቀናጀ መንገድ በማስፈጸም፣ የመንግስት አገልግሎቶችን ዘመናዊ በማድረግ፣ የተቋማትን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት በማጠናከር፣ የሰው ኃይል አቅምን በማሳደግና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በጉባኤው የተነሱ ሀሳቦችና አቅጣጫዎች በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውስጥ እንዲካተቱ በመወሰን፣ የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይን በጎፋ ዞን በተጨባጭ ውጤት ለማሳካት ሁሉም ተቋማት በቅንጅት፣ በኃላፊነትና በቁርጠኝነት እንዲሰሩ በመግባባት መድረኩ ተጠናቋል።
የጎፋ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን እውን ለማድረግ ሁሉም ተቋማት በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል" አሉ አቶ ይሁን ደምሴ