የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው
ሣውላ፤ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ የውይይት መድረክ በሣውላ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ፣ የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።
የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጎፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ እንደገለፁት፣ በ2018 በጀት ዓመት የጤናው ዘርፍ በሁሉም የአገልግሎት መዋቅሮች ጉልህ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
በተለይም የጤና ተቋማትን የማስፋፋትና የግንባታ ስራዎችን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት በርካታ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ገልፀዋል።
አያይዘውም በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በተደረገው የቅንጅት ስራ የተመዘገበው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም በሽታውን ለማስቀረት ሁሉም አካላት የተጠናከረ የቅንጅት ስራ ማከናወን እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሲስተር አሚናት ሰይድ በበኩላቸው፣ የ2018 በጀት ዓመት የዞኑ የጤና ዘርፍ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
ለዚህ ውጤት መሳካት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርና ትብብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ጠቁመዋል።
ሲስተር አሚናት አክለውም፣ በአንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ በቅንጅት፣ በትብብርና የተቋማትን አቅም በማጠናከር በከፍተኛ ደረጃ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀው፣ የበሽታውን ስርጭት በዘላቂነት ለመከላከል ማህበረሰቡ ለአካባቢ ፅዳት እና ለበሽታ መከላከል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በውይይት መድረኩ የጎፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ፣ የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ፣ የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሲስተር አሚናት ሰይድን ጨምሮ የከተማና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የከተማና የወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የዞኑ የጤና ማኔጅመንት አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የጎፋ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው