የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ በአርባ ምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉባኤው የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም በዋና ዋና የልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ላይ በማተኮር ለምክር ቤቱ በዝርዝር የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡

ጉባኤው በዛሬው ውሎ በርዕሰ መስተዳድሩ የሚቀርበውን የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በማድመጥ በዝርዝር የሚወያይ ከመሆኑም ባሻገር፤ የምክር ቤቱን የ6ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤ መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምክር ቤቱ ከሐምሌ 17 እስከ 18/2018 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚያካሂደው በዚሁ ጉባኤው፡-

የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ፤ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የቀረበን የክልሉን መንግስት የ2019 ረቂቅ በጀት፤ ክልላዊ ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር የክልሉን ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆች መርምሮ ማፅደቅን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጉባኤው በሁለት ቀን ቆይታው የክልሉ መንግስት ለክልላዊ የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ራዕይ ስኬት በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማከናወን ላይ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የሰላም፤ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች ያስቀምጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ጉባኤው የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት አባላት ባለፉት አምስት ዓመታት ለክልሉ ሕዝቦች በጋራ የመልማት ትልም ስኬት እና ለሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ውሳኔዎች በማሳለፈና በህዝብ እንዴራሴነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ስለመወጣቸው ዕውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባኤው የክልሉ ሕዝብ ም/ቤት አባላት፤ የክልሉ አስፈጻሚ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፤ የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አካላት፤ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

#ርዕሰመስተዳድርጽቤት