የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ የውይይት መድረክ ተጠናቀቀ

የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ የውይይት መድረክ በሣውላ ከተማ ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ተጠናቋል።

በመድረኩ የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ እንደገለጹት፣ በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገበው የጤና ዘርፍ አፈፃፀም የተሻለ ቢሆንም፣ በህፃናት የሥርዓተ-ምግብ እጥረት ምክንያት የሚደርሱ ሞቶችና በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ የወባ ወረርሽኞች አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አያይዘውም የዞኑ መንግስት በበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ ለጤና ተቋማት የተለያዩ የቁሳቁስና የአቅም ማጎልበቻ ድጋፎችን ማድረጉን ገልጸው፣ ሆኖም በአንዳንድ የጤና ተቋማት የታየው ዝቅተኛ አፈፃፀም በአጠቃላይ የሪፖርቱን ውጤት እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሲስተር አሚናት ሰይድ በበኩላቸው፣ በ2018 በጀት ዓመት በመከላከል ዘርፍ የተሻለ ሥራ መሰራቱን ገልጸው፣ ነገር ግን በአየር ጠባይ መዛባትና በአንዳንድ ተቋማት የታየ የዕቅድ አፈፃፀም ዝቅተኝነት ተግዳሮት መፍጠሩን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በአንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ በተቋማት ቅንጅትና በባለድርሻ አካላት ትብብር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው፣ ወረርሽኙ ዳግም እንዳይከሰት ማህበረሰቡ የአካባቢ ንፅህናን በትኩረት መጠበቅና የወባ መራቢያ ስፍራዎችን ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በአንዳንድ መዋቅሮች የዕቅድ አፈፃፀምና የመረጃ ሪፖርት አቀራረብ ወጥነት እንደሌለው ጠቁመው፣ በቀጣይ የመረጃ ጥራትን ማሻሻል፣ የተቋማትን ቅንጅት ማጠናከርና በጋራ በመስራት የጤና አገልግሎትን የበለጠ ማሻሻል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ኤልያስ፣ የጎፋ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ፣ የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሲስተር አሚናት ሰይድን ጨምሮ የወረዳና የከተማ አስተዳዳሪዎች፣ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊዎች፣ የወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የጤና ማኔጅመንት አካላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
በመጨረሻም በጤና ተቋሙ ለበርካታ ዓመታት በማገልገል በጡረታ ለተገለሉ ባለሙያዎች የዕውቅና ምስክር ወረቀት በመስጠት ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

የጎፋ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት