የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ
ሣውላ፦ ነሐሴ 3/2018 ዓ.ም
የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ በሣውላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ላይ የጎፋ ዞን ዋና አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ሀብታምነሽ ግራዝማች ተገኝተው እንደገለጹት፣ ምክር ቤቶች የሕዝብን ሉዓላዊነት በማስከበርና የሕዝብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የሚጠበቅባቸውን የክትትልና ቁጥጥር ሚና በተገቢው በመወጣት እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ምክር ቤቱ በአስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው አካላት አፈጻጸም ላይ በሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር፣ እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር በሚያደርጋቸው የአስተያየት መስጫ መድረኮች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍትሄ እየተሰጣቸው መሆኑን አፈ-ጉባኤዋ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ በባለሙያ እንዲደገፍ በማድረግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖችም በራስ አቅም ፈጣን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስና የማኅበረሰብ መተጋገዝን ለማጎልበት የተጀመረው የሀብት ማሰባሰብ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ክብርት ወ/ሮ ሀብታምነሽ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል፣ በሕዝብ አስተያየት መድረኮች የመንግሥት ሠራተኞች በተቀመጠው የአገልግሎት ደረጃ መሠረት አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው በስፋት መነሳቱን ጠቁመው፣ በ2019 በጀት ዓመት ችግሮቹን በመለየት የመፍትሄ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ምክር ቤቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተቋማት በመሆናቸው፣ በምርጫ ሂደት ውስጥም በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ምርጫዎች በነፃነት፣ በገለልተኝነትና በብቃት መከናወናቸውን ማረጋገጥ ከሚጠበቅባቸው ኃላፊነቶች መካከል እንደሆነ አፈ-ጉባኤዋ አስታውቀዋል።
በጉባኤው የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ፣ የምክር ቤቱ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጉባኤው በምክር ቤቱ ምክትል አፌ-ጉባኤ በክቡር አቶ ቦረና ቦኖ አማካኝነት የአፈፃፀም ሪፖርት እና የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ እየቀረበ ይገኛል።
በቀጣይም በጉባኤው የተለያዩ የአፈጻጸም ሪፖርቶች፣ የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅዶችና የበጀት ረቂቅ አዋጆች ቀርበው በምክር ቤቱ አባላት ውይይት ተደርጎባቸው እንደሚፀድቁም ይጠበቃል።
የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ መካሄድ ጀመረ