የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የሉፄ ሞዴል ትምህርት ቤት ባስመዘገበው ውጤት የደስታ መልዕክት አስተላለፉ
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የጎፋ ልማት ማህበር በማቋቋም እና በመደገፍ እየሰራ የሚገኘው ሉፄ ሞዴል ትምህርት ቤት በ12ኛ ክፍል ፈተና ላስመዘገበው አበረታች ውጤት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በመልዕክታቸው፣ የሉፄ ሞዴል ትምህርት ቤት በ12ኛ ክፍል ፈተና ያስመዘገበው ውጤት የጎፋ ዞን በትምህርት ዘርፍ ላይ እየሰጠ ያለውን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን፣ የጎፋ ልማት ማህበር በትምህርት ዘርፍ በሪፎርምና በተግባር ያሳየው ቁርጠኝነት ውጤት መስጠት መጀመሩን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞዴል የሚባል ውጤት ማስመዝገቡ፣ በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት ሲሰራ የሚገኝ ውጤት ምን ያህል የላቀ ሊሆን እንደሚችልም ያሳያል ብለዋል። ይህም በዞኑ የሚገኙ ሌሎች ትምህርት ተቋማት ከተመዘገበው ልምድ በመነሳት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማነሳሳት የሚችል ተሞክሮ መሆኑንም አመልክተዋል።
የጎፋ ዞን አስተዳደር በቀጣይም የሉፄ ሞዴል ትምህርት ቤት የተመዘገበውን ውጤት ከፍ በማድረግ በትምህርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ፣ ማለትም 100 በመቶ ወደ ቀጣይ የትምህርትና የሥራ ዕድል ለማሸጋገር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እገዛ እንደሚያደርግ ኢንጂነሩ ገልጸዋል።
በተለይም የጎፋ ልማት ማህበር ትምህርት ቤቱን በማቋቋምና በማጠናከር የጀመረውን ጥረት ማጠናከር፣ የትምህርት ጥራትን ማሻሻልና የተመዘገበውን ውጤት በዘላቂነት ማስቀጠል የሚቻለው በተቋሙ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች፣ በወላጆች፣ በመምህራን፣ በተማሪዎችና በልማት አጋሮች የጋራ ትብብርና አንድነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በመልዕክታቸው ለተመዘገበው ውጤት የትምህርት ቤቱን አመራር፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወላጆችና የጎፋ ልማት ማህበርን በማመስገን፣ ይህ ውጤት የጎፋ ሕዝብ በልጆቹ ትምህርትና በቀጣይ ትውልድ ላይ ያለውን ተስፋ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
የተጀመረው ጥሩ አፈጻጸም በቀጣይ የተሻለ ውጤት እንዲያፈራ በትምህርት ጥራት፣ በተማሪዎች ድጋፍ፣ በመምህራን አቅም ማሳደግና በትምህርት አመራር ላይ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የሉፄ ሞዴል ትምህርት ቤት ያስመዘገበው ውጤት የጎፋ ዞን የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እያደረገ ላለው ጥረት አበረታች ምልክት መሆኑን በመግለጽ፣ ውጤቱ እንዲቀጥልና ከዚህም በላይ እንዲሆን ሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች የልማት ማህበሩንና ትምህርት ቤቱን በጋራ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የሉፄ ሞዴል ትምህርት ቤት ባስመዘገበው ውጤት የደስታ መልዕክት አስተላለፉ