የኮረሪማ ልማት የአርሶአደሩን አደሩን ገቢን ከማሳደግ ባለፈ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን እያጠናከረ መሆኑ ተገለፀ

በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ ቶባ ቀበሌ የተካሄደው የኮረሪማ ልማት የአርሶ አደሩን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃንና ዘላቂ ልማትን በተግባር እያጠናከረ መሆኑ ተገለጸ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ የተመራው የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በመሎ ኮዛ ወረዳ ቶባ ቀበሌ በሚገኝ የሞዴል አርሶ አደር ማሳ በመገኘት የኮረሪማ ምርት ምልከታ አድርጓል።

ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ በምልከታው ወቅት እንደገለጹት፣ የኮረሪማ ልማት ከፍተኛ የገቢ አቅም ካላቸው የግብርና ምርቶች አንዱ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ የተሻለ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ይገኛል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የኮረሪማ ልማት ከኢኮኖሚ ጥቅሙ ባለፈ ተራራማ አካባቢዎችን ከመሸርሸር በመጠበቅ፣ የመሬት ናዳና መንሸራተትን በመከላከል እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ዘላቂ ልማትን የሚያጠናክር ነው።

በቶባ ቀበሌ የታየው የኮረሪማ ልማትም የ«አረንጓዴ አሻራ»ና «አካባቢ ጥበቃ ለሁለገብ ብልጽግና» እሳቤዎችን በተግባር ያረጋገጠ ተሞክሮ መሆኑን ዶ/ር መሪሁን ገልጸዋል። አካባቢን ሳይጎዱ ሀብት ማፍራት፣ የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግና የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ በአንድ ላይ ሊሳካ እንደሚችል በመስክ የታየው ልማት ማሳያ መሆኑንም አመልክተዋል።

ይህ ተሞክሮ በሌሎች አካባቢዎችም በስፋት ተደግሞ እንዲተገበር ማድረግ የግብርና ምርታማነትን፣ የገቢ አቅምንና የአካባቢ ጥበቃን በአንድ ላይ ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው፣ በዞኑ የቅመማ ቅመም ልማትን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ የኮረሪማ ልማት ከምርት መጠን መጨመር ባለፈ የገበያ ትስስርንና የአርሶ አደሩን ገቢ በማጠናከር ለዞኑ ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለው ሚና እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

በቶባ ቀበሌ የሚገኘው ሞዴል አርሶ አደር በበኩሉ የኮረሪማ ልማትን በስፋት በማከናወን በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ ከምርቱ ሽያጭ እንደሚያገኝ ገልጿል።

በአጠቃላይ በቶባ ቀበሌ የታየው የኮረሪማ ልማት የአርሶ አደሩን የገቢ አቅም በማሳደግ፣ የገበያ ትስስርን በማጠናከርና የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የተጠናከረ እና ዘላቂ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ የግብርና ልማት ተሞክሮ መሆኑ ተገልጿል።