ፍትህ የጥቂት ሰዎች ችሮታ ሳይሆን የሁሉም ሰው መብት በመሆኑ የተሰጠንን ኃላፊነት በተገቢው መወጣት ይገባል – አቶ ፀጋዬ ፅጌ
የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት አካሄደ።
መድረኩ በበቶ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ ከሁሉም መዋቅሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። መድረኩን የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ፀጋዬ ፅጌ መርተዋል።
አቶ ፀጋዬ ፅጌ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሰጡት ማብራሪያ፣ የጎፋ ዞን ፍርድ ቤቶች በ2018 በጀት ዓመት የዳኝነት አገልግሎትን ፍትሐዊ፣ ተደራሽ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ አቅደው በርካታ ሥራዎችን ማከናወናቸውንና አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።
“ፍትህ የጥቂት ሰዎች ችሮታ ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ መብት ነው። በመሆኑም የተሰጠንን ኃላፊነት በተገቢው መንገድ መወጣት ይገባል” በማለት አፅንዖት ሰጥተዋል።
በበጀት ዓመቱ የጎፋ ዞን ፍርድ ቤቶች የወንጀልና የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ጨምሮ በድምሩ 21,658 መዝገቦችን ተቀብለው 20,901 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠታቸው ተገልጿል። ይህም የመወሰን አቅም 96.50 በመቶ እንዲደርስ ማድረጉን አቶ ፀጋዬ ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶች ዜጎች ፍትህን የሚያገኙበት አደባባይ በመሆናቸው፣ የሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎትም በየጊዜው እየተሻሻለ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ፍትሐዊ ፍትህ ማለት ማንም ሰው በቋንቋ፣ በሀብት፣ በሥልጣን፣ በሃይማኖት ወይም በዘር ልዩነት ሳይደረግበት በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነ ተረድተን መፈጸም ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የዜጎች የመደመጥ መብት እንዳይጣስ፣ በፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የተሰማሩ የዳኝነት አካላትና ሌሎች ሠራተኞች ያለመታከት መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በተለይም የሕግ ዕውቀት ለሌላቸው ዜጎች በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ተገቢውን ድጋፍና ትብብር በማድረግ የፍትህ መዘግየትን መከላከል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው፣ የቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ሁሉን አቀፍና የየዘርፉን አፈጻጸም ያካተተ በመሆኑ አፈጻጸሙ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የቀጣይ ዕቅዶችን በተሻለ መንገድ ለመፈጸምም በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም የታዩ ክፍተቶችን በመለየትና በመፍታት በቅንጅትና በትብብር ለውጤት በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በ2018 በጀት ዓመት ከ1ኛ -3ኛ በመውጣት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፍርድ ቤት መዋቅሮች የዕውቅና ዋንጫና የምስክር ወረቀት በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል።
ፍትህ የጥቂት ሰዎች ችሮታ ሳይሆን የሁሉም ሰው መብት በመሆኑ የተሰጠንን ኃላፊነት በተገቢው መወጣት ይገባል – አቶ ፀጋዬ ፅጌ