"በክልሉ ሕጋዊ የንግድ ስርዓትና ተወዳዳሪነትን በማስፈን የተረጋጋ ኢኮኖሚን ለመገንባት መረባረብ ይገባል" አቶ ተፈሪ አባተ
በበጀት ዓመቱ 156 መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ስራ እንዲገቡ መደረጉም ተመላክቷል
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በክልሉ ሕጋዊ የንግድ ስርዓትና ተወዳዳሪነትን በማስፈን የተረጋጋ ኢኮኖሚን ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል
የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ አበርክቶ ያለው በመሆኑ በቁርጠኝነት መምራት ያስፈልጋል ሲሉም ኃላፊው አመላክተዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ከተኪ ምርት ባሻገር የኤክስፖርት ምርትን እንዲያመርቱ በበቂ ሁኔታ ሊደገፉ እንደሚገባ የገለፁት ኃላፊው ነፃ ገበያን ከመርህ ውጭ በሚተገብሩ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በክልሉ ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከስራ ቦታ፣ ግብዓቶች እንዲሟሉ ከማድረግና የሊዝ ፋይናንስ ችግሮችን መቅረፍ ይገባል ያሉት አቶ ተፈሪ የጠቅላይ ሚንስሩ ኢንሼቲቭ የሆነውን የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን የማስፋት ስራ አፅንኦት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት አመት የኢንዱስትሪ ዘርፉን በልዩ ሁኔታ በመደገፍ 22 መካከለኛ እና 134 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ስራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያፈሩ 2 መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸውን የገለፁት ኃላፊዋ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለይቶ በመፍታት ክልላዊ የማምረት አቅም 63 በመቶ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 5 አዳዲስ የስንበት ገበያዎች በመክፈት በክልሉ የሚገኙ አጠቃላይ የሰንበት ገበያዎችን 105 ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል።
ፍትሐዊ ገበያ ምህዳር ለመፍጠር በተሰራ ስራ በ2018 በጀት ዓመት በ2 ሺህ 467 ሕግ ባላከበሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር 5 የንግድ ፈቃዶችን መሠረዙን ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን ተናግረዋል።
የቢሮው የ2018 በጀት አመት አፈፃፀም እየቀረበ ሲሆን ውይይት ይደረጋል ተብሎም ይጠበቃል።
"በክልሉ ሕጋዊ የንግድ ስርዓትና ተወዳዳሪነትን በማስፈን የተረጋጋ ኢኮኖሚን ለመገንባት መረባረብ ይገባል" አቶ ተፈሪ አባተ