በሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል አንዲት እናት አራት ህፃናትን በሰላም ተገላገለች

ነሐሴ 24 ቀን 2018 ዓ.ም

በጎፋ ዞን ሣውላ አጠቃላይ ሆስፒታል አንዲት እናት በአንድ ጊዜ አራት ህፃናትን በሰላም መገላገሏ ተገለጸ።

እናቲቱና አራቱም ህፃናት በአሁኑ ወቅት በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ከሆስፒታሉ ተገልጿል።

የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር ግላንደ ጊሎ እንደገለጹት፣ በሆስፒታሉ ደረጃ ሁለትና ሦስት ህፃናትን በአንድ ጊዜ ማዋለድ የተለመደ ቢሆንም፣ በአንድ ወሊድ አራት ህፃናትን በሰላም ማዋለድ መቻሉ በሆስፒታሉ የመጀመሪያ ጊዜ ነው ብለዋል።

የተቀናጀ ድንገተኛ ቀዶ ሕክምናና የማህፀን ሐኪም ደመቀ ይርጋው በበኩላቸው፣ እናቲቱ በነበረችበት አካባቢ መደበኛ የእርግዝና ክትትል ሳታደርግ ቆይታ፣ ያልተለመደ የጤና ሁኔታ ሲያጋጥማት ወደ ሆስፒታሉ መምጣቷን ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ ተገቢው ምርመራ ከተደረገላት በኋላም ለተከታታይ አምስት ቀናት በቅርብ የሕክምና ክትትል ስር ቆይታ፣ አራቱንም ህፃናት በሰላም መገላገሏን ገልጸዋል።

የአራቱ ህፃናት አባት አቶ ናፍቆት ቡሼ፣ ከዚህ ቀደም አምስት ሴት ልጆች እንዳሏቸውና ባለቤታቸው በአሁኑ ወሊድ ደግሞ አራት ሴት ህፃናትን መገላገሏን ተናግረዋል።በዚህም በድምሩ የዘጠኝ ሴት ልጆች አባት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች በመሆናቸው የተሰጣቸውን በደስታ እንደሚቀበሉ የገለጹት አቶ ናፍቆት፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ያላቸው አቅም ውስን በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

እናቲቱ ወ/ሮ አንድነት አማረ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም አምስት ልጆችን መውለዳቸውን ገልጸው፣ በአንድ ጊዜ አራት ህፃናትን መገላገላቸው ለእርሳቸውም ያልተለመደና እንግዳ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ አንድነት፣ ለእርሳቸውና ለህፃናቱ ሕይወት የተረባረቡትን የሆስፒታሉ ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች አመስግነዋል።

ቤተሰቡ በተለይም አራቱን አዲስ የተወለዱ ህፃናት ጨምሮ ዘጠኙን ልጆች በአግባቡ ለማሳደግ እንዲችል የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉለትም ጥሪ ቀርቧል።