በድህረ ምርጫ ወቅት ዘላቂ ሠላምን ለማፅናት ለባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ

ሣውላ፣ ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

“Community Dialogue During the Post-Election Period for Sustainable Peace Building” በሚል ርዕስ በድህረ ምርጫ ወቅት ዘላቂ ሠላምን በማስፈን ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ስልጠና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጎፋ እና ከባስኬቶ ዞኖች ለተወጣጡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሰጠ።

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፣ 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና በመጫወታቸው አመስግነዋል።

ኢንጂነር ዳግማዊ እንደገለፁት፣ በምርጫው ወቅት ሀገሪቱ ወደ ችግርና ብጥብጥ እንድትገባ እኩይ ዓላማ ይዘው የተንቀሳቀሱ አካላት ዕቅድ በኢትዮጵያውያን ሠላም ወዳድነትና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነት የተሞላበት ተሳትፎ ሳይሳካ ምርጫው በሠላም ተጠናቋል ብለዋል።

በድህረ ምርጫ ወቅትም ሠላሟ የተጠበቀችና የተረጋጋች ሀገርና ክልል ለማፅናት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣታቸው የጎፋ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ምስጋና አቅርበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቤነዘር ተረፌ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ፣ የድህረ ምርጫ ወቅት በበርካታ ሀገራት የተለያዩ ፖለቲካዊና ፀጥታ ችግሮች መነሻ የሚሆን ወቅት መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ግን ሠላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠርና እንዲጠበቅ ዜጎች የተወጡት ኃላፊነት እውቅናና አድናቆት እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ በድህረ ምርጫ ወቅት የህብረተሰቡን የሠላም ግንዛቤ ማጠናከር፣ ልዩነቶችን በውይይትና በመቻቻል መፍታት እንዲሁም በህብረተሰቡ መካከል ዘላቂ የሠላም ባህልን ማዳበር የመሰል መድረኮች ዋነኛ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል።

መድረኩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ በጋራ ተመርቷል።

በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ በተለይም በድህረ ምርጫ ወቅት ሠላምን የማስጠበቅ የጋራ ኃላፊነት፣ የማህበረሰብ ውይይት አስፈላጊነት፣ የባለድርሻ አካላት ሚና እና በህብረተሰቡ ውስጥ የሠላም ባህልን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።

ከጎፋና ከባስኬቶ ዞኖች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም በመድረኩ ተገኝተዋል።

የመድረኩ ዋነኛ መልዕክትም የምርጫ ሂደት በማጠናቀቅ ብቻ የማይገደብ ሲሆን፣ በድህረ ምርጫ ወቅት ሠላምን ማስጠበቅ፣ ልዩነቶችን በውይይት መፍታትና ለቀጣይ ትውልድ ዘላቂ ሠላምን ማስረከብ የሁሉም ዜጎችና ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑ በመድረኩ ተጠንክሮ ተገልጿል።

በስልጠናው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብነዘር ተረፌ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ታደሴ፣ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ አበራ እንዲሁም የክልሉ የምርጫ ቦርድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አንጁሎ ተሳትፈዋል።