የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀምሯል
ሣውላ፦ ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም
የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ በሣውላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በግምገማ መድረኩ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፣ የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል እንስፔክተር ሀይሉ ወዳጆን ጨምሮ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀልና የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ኮማንደር ለማ ላቾሬ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ኮማንደር ቤርኬና ባሳ እንዲሁም የከተማና የወረዳ ፖሊስ አዛዦችና የማኔጅመንት አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የፖሊስ አባላት በቁርጠኝነትና በትጋት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመወጣት ውጤታማ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለአንዳች እንከን በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ያደረገው አስተዋፅኦ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንዳንድ ወረዳዎችና ቀበሌያት ብቅ እያሉ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችንም በአጭር ጊዜ ደርሶ በመፍታት የተመዘገቡ ውጤቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
አያይዘውም በቅንነትና በታማኝነት ማህበረሰቡን የሚያገለግሉ በርካታ የፖሊስ አባላት እንዳሉ ሁሉ፣ አልፎ አልፎ በክፍተትና በወንጀል የሚሳተፉ አባላትን በመፈተሽና በማስተካከል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የቀጣይ ዕቅድ አካል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለመለየትና ለማህበረሰቡ የተሻለ፣ ጥራት ያለውና ከአድልዎ የፀዳ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት በጋራ ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
በአሰራርና በሥርዓት በመመራት በቁርጠኝነት ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸው፣ ፖሊስ በዘንድሮው 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ሂደት ላሳየው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መከላከልና ፍሰት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ለማ ላቾሬ በበኩላቸው፣ በክልሉ የፖሊስ አገልግሎትን ወጥ በሆነ መንገድ ለመተግበርና የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማረጋገጥ በየበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የአፈፃፀም ግምገማዎች እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
በግምገማውም እስከ ታችኛው የፖሊስ አባል ድረስ በጠንካራና በደካማ አፈፃፀማቸው ላይ ግለ ሂስና ሂስ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ለውይይት የሚሆን የአፈፃፀም ሰነድ ያቀረቡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ኮማንደር ቤርኬና ባሳ በበኩላቸው፣ የአፈፃፀም ግምገማው ከሁሉም የከተማና የወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች በተውጣጡ አባላት በጋራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በመድረኩም በ2018 በጀት ዓመት የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል፣ ደካማ ጎኖችን በጥልቀት በመወያየትና በማስተካከል የቀጣይ አቅጣጫዎች በመመሪያ መሰረት እንደሚቀመጡ ተገልጿል።
የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ በሣውላ ከተማ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ በውይይቱ የተገኙ ግብዓቶችን በመያዝ ለቀጣዩ የሥራ ዘመን ጠንካራ የአፈፃፀም አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑ ተጠቁሟል።
የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀምሯል